የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ነጋዴዎች ጠቅላላ ጉባኤ አካሄደ። ነሐሴ 06/2017 ዓ.ም(አቃቂ ቃሊቲ) በጉባኤው የክ/ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና፣ የንግድ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በላይ ደምሴ፤ የከተማ አስተዳደሩ ንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ምክትል ፕረዘዳንት ኢንጂነር አበበ ጉርሜን ጨምሮ የክ/ከተማና የወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች፤ ከ12ቱም ወረዳዎች የተውጣጡ ነጋዴዎች ማህበረሰብና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል። የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አለማየሁ ሚጀና በኡባኤው መክፈቻ ክ/ከተማው በስራ አፈፃፀም ትልቅ እምርታ በማምጣት ተሸላሚ በሆነበት በጀት ዓመት ማግስት መሆኑን አስታውሰው፤ ለስኬቱ የነጋዴው ማህበረሰብ ሚና ቀዳሚ እንደነበርና በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሌብነትና ብልሹ አሰራር ችግሮች የተሳተፉ በ60 አመራሮችና 474 ባለሙያዎች በድምሩ 534 አካላት ህጋዊ እርምጃ እንደተወሰደ፣ የገቢ ግብርን በማሳደግና በማዕድ ማጋራት ተግባራት በንቃት ተሳትፎ እንደነበረው፣ በአገልግልት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ምላሽ ለመስጠት አስተዳደሩ አበክሮ እንደሚሰራ ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ም/ፕሬዘዳንት ኢንጂነር አበበ ጉርሜ በንግግራቸው የመድረኩ ዓላማ ነጋዴው መብቱንና ግዴታውን አውቆ በህጋዊ የንግድ ስርዓት ውስጥ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ አዲስ ቻንበር ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ቅርንጫፍ ከወረዳ እስከ ከተማ አስተዳደር የተደራጀ እንደሆነ፣ የምክር ቤቱን ለአባላቱ በመተዳደሪያ ደንብና መመሪያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና እንደሚሰጥ፤ ምክር ቤቱ ነጋዴው ከንግድ ስራዎች በተያያዘ የሚገጥሙትን ችግሮች ለመቅረፍ እንደሚያግዘው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በመጨረሻም ከመድረክ ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ፣ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና ደንብ ማስከበር በጋራ ከተሳታፊዎች ከንግድ ስራ ጋር በተያያዙ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተው ጉባኤውን አጠናቀዋል።